ታሪካዊው የራስ ኃይሉ ዓለም-አቀፍ መዋኛ ገንዳ በዛሬው ዕለት ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደረገ::
ራስ ኃይሉ ዓለም-አቀፍ መዋኛ ገንዳ

መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የታሪካዊው የራስ ኃይሉ ዘመናዊ መዋኛ ግንባታ ፕሮጀክት በስኬት አጠናቆ ለአገልግሎት እንዲውል አድርጓል። ኢንተርፕራይዙ የግንባታ ሥራውን ቀደም ብሎ አጠናቆ የርክክብ ሂደቱ የዘገየ ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማዕከሉን በይፋ መርቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደረጄ ኃ/ገብርኤል እንደገለጹት፤ ግንባታው በዋናነት 4,100 ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚችልና 50 በ 25 ሜትር ስፋት ያለው ዓለም-አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዋኛ ገንዳን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሕፃናት መዋኛ ገንዳ፣ የመዝናኛ ክበብ፣ የልብስ መቀየሪያ ክፍሎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሱቆች እና የፓምፕ ቤት በውስጡ የያዘ ዘመናዊ ማዕከል ነው።

ይህ ግዙፍ መዋኛ ገንዳ እጅግ ዘመናዊ የሙቀት መቆጣጠሪያ (Heating System) ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን፤ ይህም የውሃውን ሙቀት እንደ አስፈላጊነቱ በማስተካከል ለውድድሮችና ለልምምዶች ምቹ እንዲሆን ያደርገዋል። በተጨማሪም ውሃው በፊዚካላዊ፣ ኬሚካላዊ እና ባዮሎጂካዊ መንገዶች ታክሞና ተጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶለታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው ዕለት ማዕከሉ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ያደረጉ ሲሆን፤ ይህም ለከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ለመዝናኛ ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ይታመናል።